post-thumb

ፋሮ ፋውንዴሽንና የደሞዝ ጭማሪውን በተመለከተ በመስከረም ወር የተሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች

በመስከረም ወር 2018 በሃገር ደረጃ በርካታ ሃሰተኛ መረጃዎች የተሰራጩ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን የፋሮ ፋውንዴሽን ትምህርት ቤት የተመለከተው አንዱ ነው።

Duwa Alila እና Alemin Dawa በተባሉ የፌስቡክ ገጾች ላይ ትምህርት ቤቱ በክልሉ የሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች ማለትም ቤኒሻንጉል ፤ጉሙዝ፤ ሺናሻ፤ ማኦ እና ኮሞ የተባሉ ብሔረሰቦችን እያስተማረ እንዳልሆነ ወይም እንዳገለላቸው አድርገው ሃሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተዋል።

መረጃው ሃሰተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫዎች

ፋሮ ፋውንዴሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲኖረው በአሶሳ ዞን ሆሞሻ ወረዳ ደግሞ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ገንብቶ የመማር ማስተማር አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ5 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል ፡፡

ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን የሚቀበለው ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የመግቢያ ፈተና ፈትኖ ሲሆን የትምህርት ቤቱን የመግቢያ ፈተና 50 እና ከዚያ በላይ ማምጣት ሲችሉ ሲሆን ሀሰተኛ መረጃውን ያሰራጩት ገጾች ማንነታቸው ያልተገለጸ ከስማቸው ጀምሮ ፌክ አካውንት ናቸው ፡፡

በነዚህ ገጾች የሚንጸባረቁ ሀሳቦችና ፅሁፎች ግለሰብና አመራሮችን በተጋነነ መንገድ የሚተቹ እና ፖለቲካዊ የግል ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩ ናቸው። በአንዳንድ የአካባቢው ማህበረሰብ ሚነሳው ቅሬታ ደግሞ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ማቆም እንዳለበት እና ልጆቻቸው ዝምብለው ገብተው እንዲማሩ ስለሚፈልጉ ይህን መነሻ ያደረገ መልዕክት ለጥፈዋል።

 

 ትክክለኛው መረጃስ ምንድን ነው? 

በሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከ 9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተምር ሲሆን በተመሳሳይ በክልሉ ከሚገኙ ሶስቱም ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ለመግባት የ8ኛ ክፍል ፈተናን እና የትምህርት ቤቱን የመግቢያ ፈተና 50 እና ከዚያ በላይ ማምጣት የቻሉ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን በዚህ ሁኔታ እንደሚያስተምሩ የፋሮ ፋውንዴሽን ትምህርት ቤት ርዕሰ መምሀር ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ በዘር ፤በቀለም እና በሀይማኖት ሳይሆን ተማሪዎች በአቅማቸው ተለክተው ከሁሉም አይነት ብሔረሰብ የተውጣጡ ተማሪዎች እንደሚማሩበት እና በዚህም ልጆቻቸው ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተማሪ ወላጆች ነግረውናል። 

በትምህርት ቤቱ ባየነው የተማሪዎች መረጃም የቁጥር ማነስና መብዛት ካልሆነ በስተቀር የሁሉም ብሄሮች ስብጥር መኖሩን አረጋግጠናል። 

በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎችም ከክልል ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪ ናቸው ፡፡ ለአብነትም በሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በ2017 ዓ/ም 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች ውስጥ 99 በመቶ ተማሪዎች አልፈዋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች ውስጥም የክልሉ ተወላጆች መኖራቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ የፌስቡክ ገጹ ላይ አሳውቋል ፡፡

እንዲህ አይነት ፌክ አካውንቶች የተቋምን እና የግለሰብን ገጽታ ለማበላሸት ፤የግል ፍላጎትን ለማሳካትና ለማንጸባረቅ አላማ ይዘው ሀሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጫሉ ፡፡ በተለይ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰው ትምህርት ቤት በክልሉ በትምህርት ዘርፉ ተወዳዳሪ የተማረ ዜጋን ለማፍራት ከሚሰራው ስራ ባለፈ የአካባቢውን  ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የጤና ፤የውሀ ተቋማትን በመገንባትና አርሶ አደሩን በማገዝ እያበረከተ ያለውን ድጋፍ ያላገናዘበ ገጽታ ለማበላሸት የተጋራ መረጃ ነው። 

የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ስለመራዘሙ የተሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች

መንግስት ከመስከረም ወር 2018 ዓ/ም ጀምሮ ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አደርጋለሁ ማለቱን የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን  ነሀሴ ወር 2017 ዓ/ም መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ  በመስከረም ወር 2018 ዓ/ም በፌስቡክ ፤በቲውተር እና በቲክቶክ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የደሞዝ ጭማሪውን መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች አራዝሞታል በሚል ሲዘዋወር የነበረው መረጃ  ሀስተኛ መረጃ ነው፡፡

ይህን መረጃ መጀመሪያ የተመለከትነው  ጀዋር መሀመድ 3ሚሊዮን ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገጹ እና በ <X> ገጹ ላይ ነው ይህ ግለሰብ ደግሞ በብዛት በውስጥ መስመር የደረሰኝ መረጃ ነው በማለት በርካታ ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ በተለይ ገዥውን መንግስት የሚተቹ መረጃዎችን ሲያጋራ እንመለከታለን ፡፡

ይህ ሀሰተኛ ወይንም ያልተረጋገጠ  መረጃ  አክቲቪስቱ ብዙ ተከታይ ያለው ገጽ ላይ እንዳጋራ በፍጥነት ነበር ሌሎች ግለሰቦችም በስፋት ሲያሰራጩ የነበረው ይህ ደግሞ የህዝብን ቁጣ ሊያስነሳና ህዝቡ መንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው እና የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ለማሻከር ከግል ፍላጎት የመነጨ ነው ፡፡

 

መንግስት ደሞዝ ከመስከረም ጀምሮ ደሞዝ እንደሚጨምር እንዳሳወቀ ሁሉ እንደተባለው ቢያራዝምና የደሞዝ ጭማሪውን እንዲያስቀር የሚያደርግ ምክንያት ቢኖረው ህጋዊ የሆነ የተረጋገጠ መግለጫ ይሰጥ ነበር ነገር ግን ይህ አልሆነም ፡፡ የደሞዝ ጭማሪው መራዘሙን በተመለከተ የመንግስት ሚዲያዎችም አልዘገቡትም፡፡

በዋናነትም ጉዳዩ የሚመለከተው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም ከደሞዝ ጭማሪው መራዘም ጋር ተያይዞ በስዓቱ ያወጣው መረጃ የለም ፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መንግስት ያደረገው የደሞዝ ጭማሪ ተራዝሟል ተብሎ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰት መሆኑን ለሚዲያዎች አሳውቀዋል ፡፡

 በኋላ ላይ ደግሞ መንግስት ከመስከረም ወር 2018 ዓ/ም ጀምሮ ለመንግስት ሰራተኞች አድርጋለሁ ያለውን የደሞዝ ጭማሪ  ነባር ደሞዝና አዲሱን ደሞዝ እንዲሁም ግብር እና ጡረታ ተቆርጦ ካሽ የሚደርሰውን ደሞዝ የሚገልጽ መረጃ ህጋዊ በሆነ መንገድ አሳውቋል ፡፡

በዚህም መሰረት ተቋማት አዲሱን ደሞዝ አስተካክለው ክፍያ እንዲፈጽሙ አስቸኳይ ትዕዛዝ ተላልፎ አዲሱ ደሞዝ ክፍያ ተጀምሯል ፡፡ ለምሳሌ ለማንሳት ያህል አሶሳ ዩንቨርስቲ ክፍያ መፈጸሙ ተረጋግጧል።

ስለሆነም በተለይ የሚዲያ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ አዳዲስና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሚከታተለን አድማጭ ተመልካች እንዲሁም አንባቢያን ወቅታዊ ተአማኒና ትክክለኛ መረጃዎችን የማሳወቅና የማስተማር ተግባራትን እንድናከናውን  ተግባርና ሀላፊነት ተሰጥቶናል ፡፡

 

ሀሰተኛ መረጃ ዎች በሀገር ፤ በዜጎችና በሀብት ላይ የሚያደርሱትን ዘርፈ ብዙ ቀውሶች  ግምት ውስጥ በማስገባት ሀሰተኛ መረጃዎችን ባለዬ እኔን ጉዳዩ አይመለከትም በሚል ከማለፍ ይልቅ ሀሰት መሆኑን የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በማጣራት የማጋለጥና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ ነው፡፡

ፀሃፊ: ሃና መንገሻ