በሐረሪ ክልል መጠጥ እንዳይሸጥ ተከልክሏል?
በቅርቡ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች በሐረሪ ክልል መጠጥ መሸጥ ስለመከልከሉ እና ሆቴሎች ስለመዘጋታቸው የተለያዩ መረጃዎች እየተዘዋወሩ ነበር።



elizabeth kebede tafa (የጣይቱ ልጅ) በሚል ከ 31 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገፅ ላይ ይህ መረጃ ተጋርቷል።
ሐረር ላይ ሆቴሎች መጠጥ እንዳይሸጡ ተከልክለዋል የሚለው መረጃ እውነታው
ከላይ በተጠቀሰው የፌስቡክ ገፅ ላይ የተለቀቀው ይህ መረጃ ምን ያህል እውነታ አለው በሚል በተደረገው የማጣራት ሂደት መረጃው ሆን ተብሎ የግል ጥቅም ወይም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተሰራጨ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።
የክልሉ ማዘጋጃ ቤት ሀላፊ አቶ ኤልያስ ዮኒስ ለሐረሪ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ በሰጡት ግብረ መልስ መረጃዎቹ ሀሰተኛ መረጃ ናቸው ብለዋል። እነዚህ መረጃዎች ከእውነት የራቁና ሆን ተብሎ የክልሉን መስተዳድር ስም ለማጠልሸት እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ሽብርን ለመፍጠር ታስበው የተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ኤልያስ አያይዘውም የክልሉ መንግስት ምቹ የትምህርት ምህዳርን ለመፍጠር ሲባል የመጠጥ መሸጫ ሆቴሎችና ሌሎችም ተያያዥ መሰል አገልግሎቶች የሚሰጡ ድርጅቶችን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ከትምህርት ቤቶች ቢያንስ 200 ሜትር ርቀት ላይ እንዲሰሩ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ወጣቱን ትውልድ ወደ አልባሌና ጎጂ ልምዶች የሚያስገቡ የጫትና ሺሻ ቤቶች እንዲሁም የቁማር ቤቶች ላይ የመዝጋት እርምጃ እንደተወሰደ ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የሆቴል ባለቤቶችን ስለጉዳዩ በማናገር በተገኘው መረጃ መጠጥ እንዳትሸጡ የሚል ምንም አይነት እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው አረጋግጠዋል። https://www.facebook.com/share/175oszAtRh/?mibextid=wwXIfr
ስለሆነም ሐረር ላይ መጠጥ መሸጥ ተከልክሏል በሚል የሚናፈሰው መረጃ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። ህብረተሰቡን ሆን ብሎ ለማደናገርና ለማወክ እየተደረገ ያለ የጥቅም ፈላጊ ግለሰቦች ድርጊት መሆኑን በገፁ ላይ የሚለጠፉት ሌሎች መረጃዎችም ጠቋሚ ናቸው።
በመሆኑም ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት መረጃዎችን ሲመለከት ቆም ብሎ ስለ መረጃዎቹ እና ስለ መረጃው ምንጮች ሊያጣሩ ይገባል እላለሁ።
ፀሃፊ:አዩብ ካዛሊ