በባህር ዳር ከተማ በአደባባይ መፈክር ተደርጓል?
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “የባህር ዳር ፋኖ በቃ የሚል መፈክር በአደባባይ እያደረገ ነው፣ የክልሉም የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ ለመውሰድ ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው” በሚል ጽሁፍ መረጃ ተሰራጭቷል። ይህ መረጃ እውነት ቢመስልም በተደረገው መጣራት የተሳሳተ መሆኑ ተረጋግጧል።
የመረጃዎች ምንጭ እና ይዘት
የውሸት ዘገባው የባህር ዳር ፋኖ በቃ የሚል መፈክር እያሰማ ወደ አደባባይ ወጥቷል እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ኃይል እርምጃ ለመውሰድ ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው የሚል የሀሰት መረጃ በፌስቡክ የተጋራ ምስል ነው።

የማረጋገጥ እና የተገኙ ቁልፍ ግኝቶች
ከላይ የተጋራው ልጥፍ ምስል የተወሰደው በTineye reverse image ፍለጋ ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል በፈረንጆቹ 2016 ካጋራው መረጃ ነው። በgoogle reverse image check በተደረገ ፍለጋ ይኸው ምስል በ2018 በማዶቴ ድረ-ገጽ ላይ የወጣ ሲሆን ፎቶግራፉ የተነሳው በአማራ ክልል በተቀሰቀሰ ተቃውሞ 11 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ እንደሆነ የሚገልጽ ምስል ነበር።

መረጃዎችን ለማረጋገጥ Google reverse image፣ Tineye reverse image እና Bing reverse image ጥቅም ላይ ውለዋል።
የመረጃው ተጽዕኖ
ይህ የተሳሳተ መረጃ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ ግልፅ ሲሆን የሰዎች የስነ-ልቦና ሁኔታ እንዲረበሽ እና የሰላም እጦት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል። እንዲህ አይነቱ የተሳሳተ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በፍጥነት በመሰራጨቱ፣ እውነትን ማጣራት አስቸጋሪ እንዲሆንና የውሸት ትርክቶች እንዲሰፍኑ አድርጓል። በእነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያት ህዝቡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችን ያለማጣራት የመቀበል አዝማሚያ አሳይቷል። ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ የመረጃ ንቃተ ህሊና (information literacy) ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው። የመረጃ ምንጩን አለማመን፣ ቪዲዮዎችን ከቀደሙ አደጋዎች ጋር ማያያዝ እና ከመረጃ ጀርባ ያለውን እውነት መመርመርን የመሳሰሉ ጠቃሚ ክህሎቶች እንደጎደሉ መታዘብ ይቻላል።
ፀሃፊ: ሞላ ባህሩ