የጆሮ ደግፍ በሽታ መድኃኒቶችን አስመልክቶ የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች
የጆሮ ደግፍ (Mumps) ከጆሮአችን በታች ና ጆሮአችን ፈት የሚገኙ ምራቅን የሚያመነጩ የጆሮ እጢዎቻችን(parotid glands) የሚያጠቃ የቫይረስ ቁስለት ሲሆን በጣም ህመም ያለው ጆሮአችን አካባቢ እብጠት የሚያስከትል ፣ ትኩሳት፣ ድካም እና የምግብ ፍላጎት መቀነስን የሚያመጣ የህመም አይነት ነው። ይህ ህመም በኢትዮጵያ በተለያዪ ባህላዊ ህክምናዎች የሚታከም ስሆን ለአብነትም በሰንደዶ ሳር ውስጥ ሰባት ባቄላዎችን በማሳለፍ በአንገት ላይ ከ3-5 ቀናት በማሰር፤ የፍየል ሽንት እና በጠጥ አብሮ በማዋሃድ እና በእብጠት ቦታ ላይ በመቀባት በሽታውን ይፈውሳል ተብሎ ይታመናል። ይህ ጥናታዊ ሪፖርትም የአንገት በላይ ህክምና ስፔሻሊስቶችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ የባህላዊ ፈውስ ህክምና አዋቂዎችን በማማከር እና በተለያዪ አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችን በማሳተፍ፣ ባህላዊ ግንዛቤዎችን ከሳይንሳዊ ማስረጃዎች ጋር በማዋሃድ እነዚህን ባህላዊ ልማዶች ይመረምራል።

1. የሚቀርበው ምክንያት(Claim)
የጆሮ ደግፍ በስንደዶ ሳር ውስጥ ሰባት የባቄላ ፍሬዎችን በማሳለፍ እና በአንገት ላይ ከ3-5 ቀናት በማሰር፣ የፍየል በጠጥ እና የፍየል ሽንትን አንድ ላይ በማዋሃድ እብጠቱ ያለበት ቦታ ላይ በመቀባት ከዚህ በሽታ መዳንና እብጠቱንም መቀነስ ይቻላል።
ባቄላን በአንገት ላይ በማሰር ጆሮ ደግፍን ማዳን ይቻላል? ሳይንስ ስለዚህ ምን ይላል?
● ውጫዊው የቆዳችን ሽፋን (stratum corneum) ትላልቅ ውህዶች ወይም አካላት ወደ ሰውነት ውስጥ እንዳይገቡ ይከለከላል።
● የምግብ መፈጨት ሂደት፡ ሰወነታችን የትኛውንም ንጥረ ነገር ከመጠቀሙ በፊት በመፍጨት ሂደት ውስጥ እንዲያልፍ ያደርጋል ።
● የጆሮ ደግፍ የቫይረስ ህመም ነው:: የሚያጠቃው ጆሮአችን አካባቢ ያሉ የፓራቶይድ ከረጢቶችን(glands) ሲሆን እነዚህ ከረጢቶችም የሚገኙት የሰውነታችን ውስጠኛው ክፍል ውስጥ ነው ።
እውነታው(fact): ውሸት ነው? ለምን? ባቄላ (Broad beans) ለጤና ጠቃሚ የሚሆነው ስንመገበው እና ሲፈጭብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ባቄላን ውጫዊ ሰውነታችን ላይ በማሰር ሰውነታችን ንጥሬ ነገሮችን እንዲያገኝ ማድረግ አይቻልም ፤ አይደለም አንገት ላይ ማሰር ተመግበን ራሱ ጆሮ ደግፍን ማዳን እንደሚቻል የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም።
2. የሚቀርበው ምክንያት(claim)፡ የፍየል ሽንት እና የፍየል በጠጥን በማዋሃድ እና እብጠቱ ያለበት ቦታ ላይ በመቀባት የጆሮ ደግፍ በሽታን ማከም እና እብጠትን መቀነስ ይቻላል።
ያነጋገርኳቸው ባህላዊ ሃኪሞች በጣም የሚገማ ፍየል የሸናበት አፈርን ጭምር በመውሰድና በመቀባት መዳን ይቻላል ካልተቀባ ግን ቆዳው ያበጠበት ቦታ ላይ ተሸብሽቦ ይቀራል በማለት መልሰዋል ።
የፍየል ሽንት በውስጡ ምን ይዟል?
● ውሃ፣ ዩሪያ፣ ክሬቲኒን፣ ማዕድናት፣ ጨው እና ቆሻሻ ምርቶችን፤
● በተጨማሪም ጎጂ ባክቴሪያዎችን፤ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን እና በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ይይዛል።
የፍየል በጠጥ በውስጡ ምን ይዟል?
● ያልተፈጨ የእፅዋት አካል፣ ፋይበር እና ቆሻሻ፤
● ከፍ ያለ የ ባክተሪያ መጠን (E. coli, Salmonella, and helminths):
● በሰዎች ላይ ከባድ ቁስለትን (infections) ሊያስከትሉ የሚችሉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን፤
እብጠቱ ያለበት ቦታ ላይ የፍየል ሽንት እና በጠጥን በመቀባት የጆሮ ደግፍ በሽታን ማከም እና እብጠቱን መቀነስ ይቻላል ?
1. የፍየል ሽንት እና በጠጥ ከፍየሉ ሰውነት ውስጥ የወጡ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን እና በሽታ አምጪ ተህዋሲያን የያዙ ቆሻሻዎች ናቸው፡፡
2. የፍየል ሽንት እና በጠጥ ቫይረሱን አያጠፋም፤ ይልቁንም የጆሮ ደግፍ በሽታው ሰውነታችን ውስጥ እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡
3. ከማዳን ይልቅ አዳዲስ ቁስለትን ያመጣል፤ እነሱን መጠቀም ለባክቴሪያ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል፡፡
4. እንደ ዓለም ጤና ድርጅት(WHO)፣ CDC እና የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያሉ የጤና ድርጅቶች ክትባትን፣ እረፍትን እና ፈሳሾችን ለጆሮ ደግፍ ህመም እንድንወስድ ይመክራሉ፡፡
እውነታው(facts) : ውሸት ነው? ለምን?
የፍየል በጠጥ እና የፍየል ሽንት የጆሮ ደግፍ በሽታን እንደሚፈውሱ ወይም በሽታን የመከላከል አቅምን እንደሚጨምሩ የሚያሳይ ምንም አይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም፡፡ ይልቁንም እነሱን መገናኘት የቆዳ ኢንፌክሽን ፤ ተቅማጥ እና ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን (zoonotic infections) ጨምሮ ከፍተኛ የጤና አደጋዎችን ያስከትላል። እናም የጆሮ ደግፍ(mumps) በሽታ ውጤታማ የመከላከያ ዘዴው ከትባትን (MMR Vaccine) መውሰድ ነው።.
አለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች እና ታማኝ የዜና ምንጮች ስለ ጆሮ ደግፍ ህመም ምን ይላሉ?
● WHO,CDC, Ethiopian Ministry of Health: ጆሮ ደግፍ የቫይረስ ኢንፌክሽን ነው። ባቄላ፣ የፍየል ሽንት ወይም በጠጥ አይከላከሉትም ። ብቸኛው የተረጋገጠ የመከላከያ ዜደ ከትባትን (MMR VACCINE) በመውሰድ ነው ስሉ አስነብበዋል፡፡.
● Fana Television (YouTube, 1.79M+ subscribers): የህጻናት የ ጤና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ቤዛዬ አቤቤ ፋና ቴሌቪዥን ላይ በመቅረብ በአንገት ላይ ባቄላን ማሰር የጆሮ ደግፍ በሽታን ለማዳን ምንም አይነት የህክምና ጠቀሜታ የለውም በማለት አብራረተዋል፡፡ የሰው ልጅ በአእምሮው እድናለሁ ሲልና ሲያምን የመሻሻል ምልክቶችን ማሳየት እንደሚጀምርና የጆሮ ደግፍ በሽታውም የሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም ሲጨምርይጠፋል ስትል አብራርታለች።
● Addis Media Network (185K+ subscribers): ዶ/ር ኦሊያድ ታረቀኝ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ በመቅረብ የጆሮ ደግፍ ህመም እረፍት በማድረግ፣ ፈሳሽ እና የህመም ማስታገሻዎችን በመውሰድ መከላከል ይቻላል ስሉ አስረድተዋል፡፡
● SNNPR Health Bureau፡ የሕፃናት ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አላምረው አለባቸው የደ.ብ.ብ.ህ.ክ.መ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ጆሮ ደግፍ የቫይረስ ኢንፌክሽን መሆኑን ሕክምናውም እረፍት ማድረግ፤ ፈሳሽ መውሰድ፤ የህመም ማስታገሻዎችንና ከትባትን (MMR vaccine) በመውሰድ መዳን ይቻላል በማለት አስነብበዋል።
● የሀዋሳ ሪፈራል ሆሲፒታል ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ጽዮን ግርማን በዚህ ጉዳይ ባነጋገርኳት ጊዜ የጆሮ ደግፍ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ሲሆን በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ነው። ባቄላን ማሰር ፤ የሰንደዶ ሳርን ማሰር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም በማለት መልሰዋል።
በጊዜ ያልታከሙት የጆሮ ደግፍ በሽታ የሚያመጣው አደጋ ምንድነው?
● ኦርhth(Orchitis) - የወንድ እንቁላል እጢ ማበጥ እና የመካንነት አደጋን በወንዶች ላይ ሊያመጣ ይችላል፡፡
● ኤንሴፋላይቲስ( Encephalitis) - ሞትን የማስከተል አደጋ ያለው የአንጎል ኢንፌክሽን ያመጣል፡፡
● ፓንክሪያታይተስ – የሆድ ህመምና የምግብ መፈጨት ችግርን ያስከትላል፡፡
● የመስማት ችግርን ያመጣል፡፡
ማጠቃለያ
ባህላዊ ልማዶቻችን እና ቅርሶቻችን አስፈላጊ እሴቶቻችን ናቸው። ለማህበረሰባችንም ከፍተኛ አስተዋፅዖን ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ባቄላ፣ የፍየል ሽንት እና በጠጥ ያሉ ሕክምናዎችን ለጆሮ ደግፍ ህመም መጠቀም ከማዳን ይልቅ ለቁስለት እና ለሌሎች ከባድ የጤና አደጋዎች ያጋልጣሉ፡፡ የጆሮ ደግፍ በሽታን ለመከላከል ውጤታማው ዘዴ ብዙ ፈሳሽ መውሰድ፤ እረፍት ማድረግና የኤምኤምአር ክትባትን መጠቀም ነው። ይህንን እውነታ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለሎችም የመረጃ ምንጮች ላይ የቀረቡ ሳይንሳዊ ጥናቶች በትክክል ያረጋግጣሉ። እውነተኛ ጤና የሚገኘው በትክክለኛ የጤና አገልግሎት እና በሙያዊ ዶክተሮች ምከር እና እርዳታ ነው። ስለዚህ ይህንን በመገንዘብ ሕዝባችን የጆሮ ደግፍ ህመምን በጊዜ ባለመታከም ከሚደስበት የተለያዪ የጎንዮሽ ጉዳቶች እራሱን እና ህዝቡን መጠበቅ ይኖርበታል።
ምስጋና
ለዶ/ር ጽዮን ግርማ(ከሀዋሳ) ፤አቶ ኮሻና ኮሎ(ከኮንሶ)፣ ወ/ሮ ካሰች ታደሰ(ከጂማ)፤ ፋርማሲስት ታሪኩ(ከሀዋሳ) ፤ ወ/ሮ እታግኝ (ከወላይታ)፤ ወገሻ እና ባህላዊ ሃኪም ወ/ሮ መሰለች(ከሲዳማ)፣ ኢዮቤድ(ከሻሸመኔ) እና ሌሎቻችሁም ላደረጋችሁት ትብብር አመሰግናለሁ። የምላሾች እውነተኛነትን ለማረጋገጥ የድምጽ ማስረጃው ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተልኳል፡፡
ጸሐፉ : ዲኖቴ ገዛኻኝ