ከአዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የተሰራጩ የተሳሳቱ ዘገባዎች
ከሰሞኑ የኢፌዴሪ መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በሚል ከመስከረም 2018 ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል።
ከደመወዝ ጭማሪው ጋር በተያያዘ ምን ሐሰተኛ መረጃዎች ተሰራጩ ?
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይህን መግለጫ ከሰጠበት ቀን አንስቶ ብዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ማለትም "ሁሉንም የመንግስት ሰራተኛ አካል አይመለከትም" እና "የተፈቀደው አዲሱ የደመወዝ ስኬል ይህ ነዉ" በማለት የሚዘዋወር ሀሰተኛ ምስል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በፌስቡክ ፣ ቲክቶክ፣ዩቲዩብ ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ይገኛል። ይህም ሃሰተኛ ምስል በብዙዋች ዘንድ ትኩረትን ያገኘ እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚደያዎች መረጃውን ሲያስፋፉት ተስተውሏል።

በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች “የተፈቀደው አዲሱ የደመወዝ ስኬል ይህንን ይመስላል” የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችም በርካቶችን እያሳሳቱ ይገኛሉ። መረጃዎቹ ስኬል ወጥቶላቸው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የደመወዝ ተከፋዮችን የጭማሪ ልዩነትና ለሰራተኛው ተጣርቶ የሚደርሰውን መጠን በሰንጠረዥ አግባብ ተሰርተው ለማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ የዋሉ መረጃዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች ስለ ሀሰተኛ ምስሎቹ ግብረ መልስ ከመስጠታቸው እና ከማጋራታቸው በፊት የእነዚህን መረጃዎች ተደራሽነትና የስርጭት ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ሰው ተመልክቶታል አጋርቶታልም፡፡
ለምሳሌ ‹‹ፋሲል የኔአለም›› የተባለ የፌስቡክ ገጽ ከሌሎች የተጋራውን ምስል ወስዶ በራሱ ገፅ የለጠፈውና ትንታኔ የሰጠበት ሲሆን ከ1700 በላይ የላይክ መጠን፣ ከ480 በላይ አስተያየት እና እስከ 209 የማጋራት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡በተጨማሪም ሌሎች ሶስትና አራት የማህበራዊ ሚዲ ገፆች (የፌስቡክ እና የቲክቶክ ሚዲያዎች ላይ) ተሰርቶ የተለቀቀው ምስል በርካታ እይታ እና መጋራቶችን አስተናግደዋል። ይሁንና ምስሎቹን በ factcheck google search ላይ ሲጣራ ከዚህ ቀደም ከነበረው የደመወዝ ስኬል ሰንጠረዥ የእርከን ቁጥር ከሚባሉት ስሌቶች ተቆራርጦና ተገጣጥሞ የተሰራ ነው፡፡
ይሁንና "የተፈቀደው አዲሱ የደመወዝ ስኬል ይህ ነው" በሚል የተዘዋወረው ምስል እና ብዙዎች የተመለከቱት እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው የተጋሩትም ይሁን ያጋሩት ምስል ሀሰተኛ ነው፡፡ የምስሉን እና የመረጃውን ትክክለኛ አለመሆን በመንግስታዊ ሚዲያዎችና በራሱ በፌዴራል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመግለፅ ህብረተሰቡም ይሁን የመንግስት ሰራተኛው የሀሰተኛ መረጃ ተጋሪ እንዳይሆን በግልፅ አሳውቋል፡፡
መረጃዎቹ ላይ የተጋሩት ምስሎች ምንም ምንጩ ያልታወቀ እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምንም አይነት ማህተም ያልተመታበት ሆኖ ለተፈለገው አላማ እንዲሆን ተደርጎ ተሸንሽኖ የተዘጋጀ በመሆኑ እና ይህም ለምሳሌነት እንደዚ ሊሆን ይችላል ተበለው በግለሰብ ግምት የተሰሩ ብሎም ሆን ተብሎ የተዘጋጁ መሆኑን ያመለክታል ።
በርካቶች ሲቀባበሉት የነበረው የደሞዝ ስኬል መጠኑ ይህ ነው የሚለው መረጃ ባለማወቅና አውቆ በሚደረጉ አካሄዶች የተሰራጩ ሲሆን ይህንንም ብዥታ ለማጥራት ባለድርሻ አካሉ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኮሚሽነሩ ዶክተር መኩሪያ ሀይሌ በኩል በኮሚሽኑ የማህበራዊ ትስስር ላይ መረጃዎቹ ሀሰት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የደመወዝ ጭማሪው ሁሉንም የመንግስት አካላት እንደሚያካትት የተሰጡ ማረጋጋጫዎች
በመንግስት በኩል ለመንግስት ሰራተኞች ለጸጥታአካላት፣ለተመራጮች፣ለተሿሚዎች ፣ለዳኞች ፣ለአቃቤ ህግ በድምሩ ወደ 3.3ሚሊየን ለሚሆኑ በመንግሥት ደሞዝ ለሚከፈላቸው አካላት ባለፈው አመት ከ91ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አዉጥቶ ደምወዝ ማስተካከያ ማድረጉን እና ከመስከረም 2018 ጀምሮ ለመንግስት ሰራተኞች ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ በመወሰን መንግስት 160 ቢሊየን ብር ወጪ አድርጓ የደመወዝ ማስተካከያ ያደርጋል በማለት የ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ብሎም መንግሥት የቋሚ ደሞዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስተር አህመድ ሸዴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) ላይ የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ላይ በግልጽ ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት መረጃዎች ሲወጡ ከምን እናረጋግጥ?
የመንግስት ደመወዝን አስመልክቶ ትክክለኛውን መረጃ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካኝነት ብቻ የሚወጣ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል። በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚዘዋወሩ እና ምንጫቸው ያልታወቀ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማጋራታችን በፊት መረጃዎችን በጥንቃቄ መከታተል እና ትክክለኛውን መረጃ ከምንጩ በማጣራት ማረጋገጥ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ፋክት ቼክ ዘግቧል፡፡
የተሳሳተ መረጃን የጉዳት ለመቀነስ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ እና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል። በዚህም ባለድርሻ አካላቱ ሀሰተኛ መረጃዎች ላይ በጊዜዉ ሀሰተኝነታቸውን የሚያረጋግጥ መግለጫ መስጠት ማሕበረሰቡን ሊያነቁት ይገባል፡፡
ጸሐፊዎች፡ ጌታሰው ሙላት ፣አዩብ ካዛሊ እና ሰብለ እሸቱ