post-thumb

ሞሪንጋ ወይም ሽፈራውን በተመለከተ እየተሰራጩ ያሉ ሃሰተኛ መረጃዎች

የብዙ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት የሆነችው ሃገራችን ኢትዮጵያ ለምግብነት፣ለመድኃኒትነት እና ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ የተለያዩ እፅዋቶችን የታደለች መሆኗ ይታወቃል።ከነዚህም መካከል አንዱ ሞሪንጋ ሲሆን በእኛ ሃገር  በብዛት የሚገኘው ዝርያ moringa stenopetala ይባላል። ይህ ተክል በስፋት የሚገኘው በደቡብ የሀገራችን ክፍል በተለይም በጋሞ እና በኮንሶ አካባቢ ሲሆን በተጨማሪነት በሲዳማ፣ ቦረና፣ቡርጂ፣በምስራቅ ድሬዳዋ እንዲሁም በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች ይገኛል።

የሞሪንጋ ስያሜዎችና የማህበረሰባችን አጠቃቀም ሞሪንጋ የተለያዩ የአካባቢያዊ  ስሞች ሲኖሩት ለምሳሌ በአማርኛ ሽፈራው፤በጎፋ አካባቢ ሀለኮ፤ እንዲሁም በኮንሶ አካባቢ ሸላግዳ በመባል ይጠራል።ይህንን ተክል በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ማህበረሰቦች እንደ ጎመን በመቀቀል ለምግብነት ይጠቀሙታል።በንጥረ ነገሮች የበለፀገው እና ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ የመጣው ሞሪንጋ በመዲናችን በአዲስ አበባ በዱቄት መልኩ ልክ እንደ ሻይ ቅጠል ታሽጎ በፋርማሲዎች፣ በባህል ሃኪሞችና ግለሶቦች እየተሸጠ ይገኛል።

ነገር ግን ከነዚህ የሞሪንጋ ሱቆች ወይም ግለሰቦች መካከል አብዛኞቹ አጋጣሚውን በመጠቀም የግላቸውን ጥቅም ለማስቀደም ሲሉ የተጋነኑ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ሰዎችን የማታለል ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።እነዚህም ሃሰተኛ መረጃዎች የሰዎችን ጤና ከመጉዳታቸው በተጨማሪ የገንዘብ ኪሳራ እንዲገጥማቸው ያደርጋሉ።

ሞሪንጋን በተመለከተ ያሉ ሃሰተኛ መረጃዎች

ሞሪንጋን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች ከምንላቸው ውስጥ ዋነኛው ሞሪንጋ ብዙ አይነት ስር የሰደዱ በሽታዎችን መፈወስ እንደሚችልና ይሄም በሳይንስ እንደተረጋገጠ ተደርጎ የህዝብ ጥግግት በሚታይባቸው የገበያ እና የትራንስፖርት አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃዎች ሲሰራጩ ይስተዋላል።

ለምሳሌ ከታች በምስሉ እንደምንመለከተው ኢትዮ ሞሪንጋ የተሰኘ የቴሌግራም ገጽ 11 በሽታዎችን ዘርዝሮ ሞሪንጋ ከእነዚህ በሽታዎች እንደሚፈውስ በሳይንስም እንደተረጋገጠ ጠቅሷል።በቀኝ በኩል ያለው ምስል ደግሞ የሚያሳየው በቲክቫህ ኢትዮጵያ ስም የተከፈተ ሃሰተኛ ገፅ ሲሆን በሳይንስ የተረጋገጡ የሞሪንጋ ጥቅሞች በማለት በዝርዝር አስቀምጧል።

 

ምንም እንኳን ከላይ የተዘረዘሩት አብዛኞቹ በሽታዎች ከሞሪንጋ ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም  ጥቂቶቹን በሽታዎችን በተመለከተ ግን ለምሳሌ ካንሰር እንስሳቶች ላይ ምርምር ተሰርቶበታል።ስለሆነም ብዙ ሰዎች እንስሳቶች ላይ የተሰሩትን ምርምሮች በማንበብ ብቻ በሳይንስ ተረጋግጧል እያሉ ያወራሉ።ነገር ግን አንድ መድኃኒት አንድን በሽታ ለመከላከል ወይም ለማዳን በሳይንስ ተረጋግጧል ለመባል እንስሳቶች ላይ ከመሞከሩ በተጨማሪ ብዙ ሂደቶችን ማለፍ ያለበት ሲሆን ለምሳሌ እስከ 80 ገደማ የሚደርሱ ጤነኛና ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ከተሞከረ በኋላ በመቀጠል በመቶዎች የሚቆጠሩ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ላይ ይሞከራል። በመጨረሻ እነዚህን ሂደቶች ካለፈና በምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከተፈቀደ ለመድኃኒትነት ይውላል።

ሞሪንጋን በተመለከተ እንስሳት ላይ ከተደረገው ጥናት በስተቀር እነዚህ ሂደቶች ውስጥ ስላልደረሰ በሳይንስ ተረጋግጧል የሚሉ መረጃዎች ሃሰተኛ ናቸው።

የማማለያ እና የማታለያ ቃላትን በመጠቀም ሞሪንጋን የሚያስተዋውቁ ገፆችም አሉ። ለምሳሌ ከበሽታ ነፃ ለመሆን እንዲሁም በቀላሉ ቁመትን ለመጨመር ወይም ሸንቃጣ ቁመና እንዲኖራችሁ ከፈለገችሁ እኛ ጋር ያለው ሞሪንጋ የተለየ ነው ፈጥናችሁ ግዙ በማለት የሚያስተዋውቁ ሲሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ህጋዊ ፈቃድ ሰጥቶናል እያሉ ይናገራሉ።

ከነዚህም መካከል ከ116 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ዋሌ ሞሪንጋ የተሰኘ የቲክቶክ ገፅ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።

ዋሌ ሞሪንጋን ጨምሮ ሌሎችም ሞሪንጋ ተፈጥሯዊ ስለሆነ በሚል ምክንያት በላብራቶሪ ውስጥ ከሚቀመሙ መድኃኒቶች የተሻለ በሽታዎችን የማዳን አቅም አለው ብለው ያስተዋውቃሉ። ይህንን ተከትሎ ታካሚዎች በሀኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት በማቋረጥ የከፋ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ሌላው ደንበኞችን ለማብዛት እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ እንደ ሞሪንጋ ውፍረት ለመቀነስም  ለመጨመርም ይሆናል የሚሉ የሚጋጩ  ማስታወቂያዎችን በመስራት ማህበረሰቡም ግራ ሲያጋቡ ይስተዋላል።ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ከምግብ በፊት ከተወሰደ ክብደትን ለመቀነስ ከምግብ  ጋር ከተወሰደ ደግሞ ለመወፈር በማለት አሳማኝ ያልሆነ ምክንያታቸውን ይናገራሉ።

የሃሰተኛ መረጃ ስርጭቱ ምን ያህል ነው?

እነዚህ ሃሰተኛ መረጃዎች የሚሠራጩት በስፋት አዲስ አበባ ላይ ቢሆንም በሌሎች የሀገራችን ትልልቅ ከተሞች ብሎም በገጠር አካባቢዎች በተለያየ የሃገራችን ቋንቋዎች ይሰራጫሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በሽታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንና የታካሚዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሚሰሩ ሃሰተኛ ማስታወቂያዎች በቀላሉ እና በአቋራጭ መንገድ የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያሳምኑ ስለሆኑ ማህበረሰቡም ከበሽታዎች ለማገገም ካለው ትልቅ ጉጉት የተነሳ በነዚህ ሃሰተኛ መረጃዎች ተጠቂ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ወንድም ሆነ ሴት ወጣቶች ለቁንጅናቸው እና ለአቋሟቸው እንደሚጨነቁ ስለሚታወቅ በሰው ሰራሽ አስተውህሎት የሚሰሩ ምስሎችን በመለጠፍ ልክ እንደዚህ አይነት አቋም በአጭር ጊዜ አንዲኖራችሁ ከፈለጋችሁ መፍትሄው እኛ ጋር አለ በማለት ብዙ ገንዘብ ይቀበሏቸዋል።

እነዚህ መረጃዎች የሚሰራጩት በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የህዝብ ጥግግት በሚበዛባቸው አካባቢዎችም ጭምር ነው ። ለምሳሌ በመርካቶ ገበያ የድምጽ ማጉያ መሳሪያዎችን በመጠቀም እያስተዋወቁና እያዞሩ ሲሸጡ ይስተዋላል።

ሃሰተኛ ስለመሆናቸው ማረጋገጫና ማስረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ ትምህርት ቤት በፋርማኮሎጂ(ስነመድሀኒት)እና ክሊኒካል ፋርማሲ ዲፓርትመንት አስተማሪና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን አሰፋ

"ሞሪንጋ ብዙ በሽታዎችን ማከም እንደሚችልና በሳይንስ እንደተረጋገጠ ተደርጎ የሚሰራጩ መረጃዎች ሃሰተኛ ናቸው።እንስሳቶች ላይ በተደረገ ሙከራ ብዙ ጥናቶች ተሠርተውበታል።እኔም ራሴ እንስሳቶች ላይ በሰራሁት ምርምር ምንም እንኳን በሳይንስ የተረጋገጡትን መድኃኒቶችን ያህል ባይሆንም anti-diarrheal(ፀረ-ተቅማጥ)effect እንዳለው አረጋግጫለሁ። ነገር ግን አንድ መድኃኒት በሳይንስ የተረጋገጠ መድኃኒት ነው ለመባል እንስሳቶች ላይ መሞከሩ ብቻ በቂ አይደለም።

ከዚህም ባለፈ ብዙ ሂደቶችን ማለፍ አለበት ለምሳሌ በጤነኛና ፈቃደኛ ሰዎች ላይ በሳይንሳዊ መንገድ ተሞክሮ መረጋገጥ አለበት። ሲቀጥል አንድ መድኃኒት ሳይንሳዊ መድኃኒት ነው ለመባል በውሰጡ አንድ specific የሆነ molecule(activeingridient)ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን ሞሪንጋ ከአንድ በላይ ብዙ molecules ያካትታል። ከዚህም በተጨማሪ ሞሪንጋ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ቢወሰድ የመድኃኒቱን ውጤት ይጨምረዋል የሚሉ መረጃዎችንም እሰማለሁ።ነገር ግን በሞሪንጋ እና በመድኃኒቱ መካከል የሚፈጠረው interaction ህይወትን እስከ ማጥፋት ሊያደርስ ይችላል።ሌላው ደግሞ ከEFDA ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶናል በማለት ሞሪንጋን በተሳሳተ መንገድ ሲያስተዋውቁ እንመለከታለን። ብዙ በሽታዎችን ማዳን እንደሚችል አድርገው እያስተዋወቁ እንደ መድኃኒትነት እንዲሸጡ ከEFDA ፈቃድ ይሰጣቸዋል ብዬ አላስብም።ምናልባት እንደ ተጨማሪ ምግብነት እንዲሸጡት ፈቃድ ተስጥቷቸው ይሆናል።ነገር ግን ስህተቱ የሚያስተዋውቁበት  መንገድ ነው።ስለዚህ እንደ መድኃኒትነት በሳይንስ ተረጋግጦ እውቅና እስኪሰጠው ድረስ ማህበረሰባቡ ከተሳሳቱ መረጃዎች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።"ብለዋል።

በአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባስሰልጣን የጤና ነክ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ቡድን ባለሙያ የሆኑት ምትኩ ዘነበ "EFDA ህጋዊ ፈቃድ እንደሰጠናቸው አስመስለው የውሸት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ሃሰተኛ ናቸው።ሞሪንጋ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ምግብ ይሁን እንጂ እንደ መድኃኒትነት አልተመዘገበም።ስለሆነም በሽታዎችን ያክማል የሚል መረጃ አላስተላለፍንም ህጋዊ ፈቃድም አልሰጠንም።"ብለዋል።በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን(FDA) ሞሪንጋ እንደ መድኃኒትነት ፈቃድ እንዳልሰጠው መልዕከት አስተላልፏል።ስለሆነም ሞሪንጋ በሽታዎችን እንደሚፈውስ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ለሚያስተዋወቁ ድርጅቶችና ግለሰቦች ብዙየማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችን ልኳል።ከነዚህም መካከል ከታች በምስሉ እንደምንመለከተው ግለሰቡ ለፈንገስ፣ ለቫይረስ፣ ለጭንቀት እንዲሁም ለማቃጠል ስሜት ሞሪንጋ ፍቱን ነው በማለት ያስተዋወቀ ሲሆን ይህም ግለሰብ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተልኮለታል።[1]

የአለም ጤናድርጅት ሞሪንጋ በነጥረ ነገሮች የበለፀገ ምግብ (nutritiousfood) ነው ከማለት ውጪ የትኛውንም አይነት በሽታ ያድናል የሚል መረጃ  አላስተላለፈም። በተጨማሪ መረጃዎችን የሚያሰራጩበት መንገድና የሚጠቀሟቸው የማታለያ ቃላቶች መረጃቸው ሃሰተኛ እንደሆኑ ያመለክታሉ። ለምሳሌ ዋሌ ሞሪንጋ የተሰኘው የቲክቶክ ገጽ የደንበኞችን ትኩረት ለመሳብ ምንም እንኳን በአለም ላይ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ብዛት 118 ቢሆንም ሞሪንጋ በውስጡ 192 ንጥረ ነገሮችን ይዟል ሲልገልጿል። እነዚህ ሃሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩትበት ዓላማ ምንድን ነው?አብዛኞቹ ሃሰተኛ መረጃውን የሚያሰራጩት ትርፋማነትን ለማሳደግ ነው። ምክንያቱም ሞሪንጋን የሚሸጡ ብዙ ተወዳዳሪዎች ስላሉ የተሳሳቱና የተጋነኑ መረጃዎችን በመጨመር የደንበኞችን ትኩረት በመሳብ ብዙ ደንበኞችን ማግኘት ስለሚፈልጉ ነው።

ምንም እንኳን ሞሪንጋን በመሸጥ ቀጥተኛ የሆነ ትርፍ ባያገኙም ሃሰተኛ መረጃዎችን በመልቀቅ ብዙ ተከታዮችን ካገኙ በኋላ ያንን ሚዲያ ለሌላ አላማ ማዋል የሚፈልጉም አሉ።  አንዳንድ ግለሰቦች መረጃው ሐሰተኛ መሆኑን ባለማወቃቸው ነገርግን መረጃው ለወዳጅ ዘመድ ይጠቅማል ብለው በማሰባቸው መረጃውን በሚዲያ እንዲሁም በወሬ ደረጃ ያስተላልፍሉ።የተወሰኑ የቴሌግራም ገፆች ደሞ በሞሪንጋ ስም የተከፈቱ ሆነው ነገር ግን የሚያስተላልፋት ይዘት ሃሰተኛ የአስማት፣የወሲብ እና የኤሌክትሮኒክስ ንግዶችን በማስተዋወቅ የማጭበርበር ስራ ይሰራሉ።ለምሳሌ bestmoringa እናMoringa (ሞሪንጋ)adissababaየተሰኙ ገፆች ይጠቀሳሉ።

የሃሰተኛ መረጃዎቹ መሰራጨት አሉታዊ ተጽዕኖዎች ታማሚዎች በሀክምና የታዘዘላቸውን መድኃኒት በማቋረጥ ሞሪንጋን ብቻ እንዲጠቀሙ ሲያደርጉ ሞሪንጋን ከታዘዘላቸው መድኃኒት ጋር ሊወስዱት ስለሚችሉ አስጊ ሁኔታ ላይ ይጥላቸዋል። በዚህ የኑሮ ውድነት ማህበረሰቡ ገንዘብ ከየትም ፈላልጎ ይከፍላል ነገር ግን ምንም አይነት ዋስትና የላቸውም።እነዚህ ሃሰተኛ መረጃዎች የባህል ህክምና እንዲሁም ዘመናዊ የጤና ስርዓቱን በማህበረሰቡ ዘንድ እንዳይታመኑ ያደርጋሉ።የመፍትሄ ሃሳቦች እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ መረጃዎች ሲያጋጥሙን አምኖ ከመቀበልና ለሌሎች ከማጋራት ይልቅ በመጀመሪያ የመረጃውን ትክክለኛነት ከሚመለከተው አካል ማረጋገጥ ይኖርብናል።

ስለ ሞሪንጋ በሳይንሳዊ መንገድ ሰው ላይ በደንብ ተጠንቶ መከላከል የሚችላቸው እና የማይችላቸው በሽታዎች ቢለዩ መልካም ነው።ይህ ሂደት የሰው ሀይል፣ጊዜ እና በጀት ቢፈልግም  ባሉ ዩኒቨርስቲዎችና የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ ምሁራን ድጋፍ ተደርጎላቸው በደንብ መመራመር ይኖርባቸዋል።ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በመለየት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውና ሁላችንም ሃላፊነት ወስደን ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩትን ደህንነታችን በተጠበቀ መልኩ ማጋለጥ ይኖርብናል።

ፀሃፊ: ኤርሚያስ ውበት


[1] https://www.fda.gov/inspections-compliance-enforcement-and-criminal-investigations/warning-letters/apg-seven-inc-670020-04182024 ይጠቀሙ።